ስትወደቅ (ስትሳሳት)

ኃጢአት ብትሠራ ምን ታደርጋለህ?

IRS ስም ያልተፃፈበት ደብዳቤ ደረሰው፡

የተከበራችሁ፡

ከዚህ ደብዳቤ ጋር 15,000 ብር ቼክ ይደርሳቸኋል፡፡ ባለፈው ዓመት የታክስ ተመላሼን አጭበርብሬ ወስጃለሁ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ መተኛት አልቻልኩም፡፡ አሁንም በቀላሉ መተኛት ከቸገረኝ የተቀረውን እልክላቸኋለሁ፡፡

Image

ሁላችንም ለሠራናቸው በደሎች ይቅርታ የማግኘት ፍላጎት አለን፡፡ ጥያቄው ግን፣ ይህ ይቅርታ ከየት ይገኛል ነው?

እንደ ክርስቲያን፣ ኃጢአትህ ሁሉ ይቅር ተብሏል፡፡ ያንንም ያመንከው መጽሐፍ ቅዱስህን አንብህ ነው፡፡ ሆኖም አንተ ምላሽ የሰጠኸው እንዴት ነው? በርካታ ክርስቲያኖችን የሚማክር ወዳጄ እንዲህ አለ፡ “አንዳንድ ክርስቲያኖች ኃጢአት እንደሠሩ በእውነት አያምኑም፤ ሌሎቹ ደግሞ ይቅር መባላቸውን አያምኑም፡፡”

የኃጢአታችሁንም የክርስቶስን ይቅርታም እውነትነት ተቀብላችሁ እንድትደነቁ ላግዛችሁ እወዳለሁ፡፡

የኃጢአት ምንነት

ኤርነስት ሄሚንግዌይ በአንድ ወቅት እንዲህ አለ፣ በጎ ነገር ካደረግህ፣ ከድርጊቱ በኋላ ጥሩ ስሜት ይሰማሃል፤ ክፋትን ካደረግህ፣ ከዚያ በኃላ ክፉ ስሜት ይሰማሃል፡፡ በርካቶች የሚኖሩበት ዕውቅ የኃጢአት አስተሳሰብ ያንን ይመስላል፡፡ ግን መጽሐፍ ቅዱሳዊ እይታ አይደለም፡፡ መጽሐፍ ቅዱሳዊው፣ ኃጢአት ከእግዚአብሔር መንገድ ይልቅ የራስን መንገድ መምረጥ ነው የሚለው ነው፡፡

ኃጢአት ለእግዚአብሔር ምን ያህል ክብደት አለው? ፈጽሞ ቸል አይለውም፡፡ “ዓይኖችህ ክፉ እንዳያዩ ንጹሐን ናቸው፣ ጠማምነትንም ትመለከት ዘንደ አትችልም፤” (ዕንባቆም 1፡13) “እግዚአብሔር ብርሃን ነው ጨለማም በእርሱ ዘንድ ከቶ የለም…” (1ኛ ዮሐንስ 1፡5)

ምናልባት በጣም ወሳኝ ላይመስል ይችላል፡፡ ኢየሱስ የኃጢአትህን ዕዳ ከፍሎ የለምን? እግዚአብሔር እስከ ወደደህና ለሕይወትህ አስደናቂ ዕቅድ እስካለው ድረስ ስለ ኃጢአት መጨነቅ ለምን ያስፈልጋል? ኃጢአትን በሕይወት ውስጥ እንደተፈጠረ ስህተት፣ ወይም ትንሽ ስህተት ማለት ብቻ ልትቆጥረው ይገባል፡፡

እግዚአብሔር ኃጢአትን እንዲህ ተመልክቶት አያውቅም፡፡ በአንድ ኃጢአት ምክንያት፣ አዳምና ሔዋን ከገነት ተባርረዋል፡፡ በኖህም ዘመን በኃጢአት ምክንያት እግዚአብሔር በምድር የሚኖረውን የሰው ዘር በጎርፍ አጥፍቷል፡፡ እጅግ አስከፊ ከነበረው ብልሹነታቸው የተነሳ በሰዶምና በገሞራ ከተሞች ላይ እሳትን አዝንቧል፡፡ ኃጢአት ቀደምቱን የእስራኤል ልጆች ለአርባ ዓመታት አንከራቷቸዋል፡፡

እግዚአብሔር ኃጢአትን ይጠላል፡፡ ለእኛ ግን፣ ኃጢአት መልካም ይመስላል፣ እናም እናደርገዋለን፡፡ ልክ እንደ አዳምና ሔዋን፣ ክፉውን እንደምናውቅ እናስባለን ግን በእርሱ የምንሸነፍ መሆናችንን ግን አላወቅንም፡፡ ሆኖም እንደ እግዚአብሔር አልሆንንም፡፡ እግዚአብሔር የክፉውን መኖር ያውቃል፣ እግዚአብሔር ግን ክፉ አይደለም ለክፉም ተሸንፎ አያውቅም፡፡ እኛ ግን፣ ወደ እርሱ እንሳባለን፣ በእርሱም እንሸነፋለን፡፡

በደለኛው ወገን

ኃጢአትን ባደረግህ ቁጥር፣ በውስጥህ ያለው መንፈስ ያዝናል፡፡ አንዳንድ ጊዜም የበደለኝነት ስሜት እንዲሰማህ ያደርጋል፡፡ ኃጢአትን ስታደርግ፣ በዚያች ቅፅበት ከጌታ ፈቃደ ውጪ በራስህ ፈቃድ ለመኖር መርጠሃል ማለት ነው፡፡ ያ ግን እግዚአብሔርን እንዲጠላህ አያደርገውም፡፡ አሁንም ይወደድሃል፡፡ ሆኖም ያሳዝነዋል፡ “ለቤዛም ቀን የታተማችሁበትን ቅዱሱን የእግዚአብሔርን መንፈስ አታሳዝኑ፡፡” (ኤፌሶን 4፡30) ኃጢአት ምን ያህል እንደሚጎዳህ ለመገንዘብ፣ ከእግዚአብሔር ጋር ባለህ ዝምድናና ከእግዚአብሔር ጋር ባለህ ኅብረት መካከል ያለውን ልዩነት እንመልከት፡፡

ከእግዚአብሔር ጋር ያለህ ዝምድና

  • ክርስቶስን ስትቀበል ጀምሯል (ዮሐንስ 1፡12)
  • ዘላለማዊ ነው (1ኛ ጴጥሮ 1፡3፣4)
  • በብቸኘኝነት የሚጠበቀው በእግዚአብሔር ነው፡፡ (ዮሐንስ 10፡27-29)
  • አይለዋወጠጥም (ዕብራውያን 13፡5)

ከእግዚአብሔር ጋር ያለህ ኅብረት

  • ክርስቶስን ስትቀበል ጀምሯል (ቆላስይስ 2፡6)
  • ሊታወክ ይችላል (መዝሙር 32፡3-5)
  • በከፊል የሚጠበቀው በአንተ ነው፡፡ (1ኛ ዮሐንስ 1፡9)
  • ኃጢአት ስታደርግ ይለወጣል (መዝሙር 66፡18)

ኃጢአት ከእግዚአብሔር ጋር ያለህን ዝምደና ሊያውከው አይችልም - ክርስቶስ ለኃጢአትህ ዋጋ መክፈሉን ባመንክበት ወቅት የተመሠረተ ነው፡፡ ክርስቶስ ስለ ኃጢአትህ ሁሉ ሞቷል-- ማለትም ያለፈውን፣ የአሁኑን እና የወደፊቱን ማለት ነው፡፡ በዚያን ወቅት፣ ሕይወትህ በጠቅላላ በወደፊት ጊዜ ነበር፡፡ በኢየሱስ ካለህ እምነት የተነሳ፣ ሙሉ ለሙሉ ይቅር ተብለሃል፡፡ ከእግዚአብሔር ጋር ያለህ ዝምድና የተጠበቀ ነው፡፡

ሆኖም፣ ኃጢአት ከእግዚአብሔር ጋር ያለህን ኅብረት ያውከዋል፡፡ (ኅብረት ማለት በምድር ላይ የሚከናወን በእያንዳንዲቷ የሚካሄደ ትስስር ነው፡፡) ኃጢአት ከእርሱ ጋር ያለህን ግንኙነትና የእርሱን ፈቃድ ከመፈፀም አንፃር ያለህን ጠቀሜታ ያውከዋል፡፡ ኃጢአት እንድታስበው እና እንድታደርገው ክርስቶስ የሚፈልግብህን ነገር እንዳታደርግ ያደነዝዝሃል፡፡

Image

መዝሙር 32፡3-5 እንዲህ ይላል፡ “ሁል ጊዜ ከመጮኼ የተነሳ ዝም ባልሁ ጊዜ አጥንቶቼ ተበላሹ፤ በቀንና በሌሊት እጅህ ከብዳብኛለችና፣ እርጥበቴም ለበጋ ትኩሳት ተለወጠ፡፡ ኃጢአቴን ለአንተ አስታወቅሁ፣ በደሌንም አልሸፈንሁም፤ ለእግዚአብሔር መተላለፌን እነግራለሁ አልሁ፤ አንተም የልቤን ኃጢአት ተውህልኝ፡፡”

ይህ ለኃጢአት ሊሰጥ የሚገባው ትክክለኛ ምላሽ ነው፡፡ ዘማሪው ኃጢአትን አልካደውም፡፡ አልሸፋፈነውም፡፡ ተናዝዞታል፡፡

ኃጢአትን መናዘዝና ንስሓ መግባት

ኃጢአትን መናዘዝና መተው ማለት ምን ማለት ነው? በመጀመሪያ፣ መናዘዝ ማለት ከእግዚአብሔር ጋር መስማማት ማለት ነው፡፡ እርሱ ኃጢአት እንዳደረግህ ያውቃል፣ ስለዚህ አንተም እውነተኛ ሁን! “በኃጢአታችን ብንናዘዝ ኃጢአታችንን ይቅር ሊለን ከዓመፃም ሁሉ ሊያነፃን የታመነና ጻድቅ ነው፡፡”(1ኛ ዮሐንስ 1፡9) መናዘዝ ማለት ያለ አስገዳጅ ኃጢአት እንደሠራን ማመንና ስለ እኛ ኃጢአት እግዚአብሔር ያለውን አስተሳሰብ መቀበል ማለት ነው፡፡

መናዘዝ ማለት እግዚአብሔር ይቅር እንዲለን መለማመጥ ማለት አይደለም፡፡ ክርስቶስ የኃጢአታችንን ዕዳ ከፍሏል፣ ስለዚህ በተናዘዝንበት ወቅት የእግዚአብሔር ይቅርታ ዝግጁ ሆኖ ይጠብቃል፡፡ እግዚአብሔር ይህ ይቅርታ ወዲያውኑ እንዲገኝ ያደረገበት ምክንያቱ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ስለሞተ ነው እንጂ፣ ኃጢአትህን ስትናዘዝ ባሳየኸው ጥንካሬና ትህትና ላየይ አይደለም፡፡

ንስሓ ማለት ግን ከኃጢአት ጋር ተያይዞ ያለህን ተግባር መለወጥ ማለት ነው፡፡ እንደተሳሳትህ ማመን ያንን ኃጢአት ደግመህ መሥራት እንደማትፈልግ ከእግዚአብሔር ጋር መስማማትን ያካትታል፡፡

ግን አሁንም በደለኝነት ይሰማኛል!

ኃጢአትህን ከተናዘዝክም በኋላ እንኳን የበደለኝነት ስሜት የሚሰማህ ወቅት አለ፡፡ ይህን የመሰለ አሳዛኝ ኃጢአት በመሥራታችን ራሳችንን ኩስምን ማድረግ (መኮነን) መንፈሳዊነት ይመስላል፣ እናም ራሳችንን በጣም ካዋረደነው፣ እግዚአብሔር በእኛ የትህትና እርምጃ ደስ ይሰኛል ብለን እናስባለን፡፡

እግዚአብሔር እኛን የሚያየው ግን እንደዚያ አይደለም፡፡ የኑዛዜ አንዱ ክፍል የኃጢአት እዳችን በክርስቶስ ስለተከፈለ ማመስገን ነው፡፡ በዚያ መሠረት እግዚአብሔር እንዲህ ብሏል፣ “ዓመፃቸውን እምራቸዋለሁና፣ ኃጢአታቸውንም ደግሜ አላስብም፡፡” (ዕብራውያን 8፡12) ምሥጋና የእግዚአብሔር ቃል ስለ አንተ የተናገረው እንጂ አንተ የሚሰማህ አለመሆኑን በማወቅ ምላሽ መስጠትን ያካትታል፡፡ ራስን መኮነን በክርስቶስና በይቅርታው ላይ ከማትኮር ይልቅ በራስህ ላይ እንድታተኩር ያደርግሃል፡፡

Image

አንዳንድ ጊዜ መፈተንን ከኃጢአት ጋር እናምታታዋለን፡፡ ሆኖም ሁሉም እንደሚፈተን ልብ በሉ፡፡ ኢየሱስ እንኳን ተፈትኗል … ሆኖም ለፈተናው ግን እጁን አልሰጠም - እርሱ ኃጢአትን አላደረገም፡፡ ስትፈተን ራስህን፣ አትቅጣ፡፡ ፈታኝ በሆኑ ሃሳቦችህ ተይዘህ አለመቆየትን ምርጫህ አድርግ ደግሞም ኃጢአትን አሻፈረኝ ማለት የምትችልበትን አቅም እንዲሰጥህ እግዚአብሔርን ለምን፡፡ በፈተንህ ራስህን አትኮንን፡፡ ከፈተና ጋር ግብግብ ስትገጥም፣ ልብ ልትለው የሚገባ ጥቅስ፣ 1ኛ ቆሮንቶስ 10፡13 ነው፡፡

የሠራኸውን ነገር ሁሉ እግዚአብሔር ይቅር ብሎሃል፡፡ “እንግዲህ በክርስቶስ ኢየሱስ ላሉት አሁን ኩነኔ የለባቸውም፡፡” (ሮሜ 8፡1) ኃጢአትህን ወይም ውድቀትህን ወደኋላ እያሰበ በኩነኔ አይመለከትህም፣ እናም አንተም እንደርሱው ልታደርግ ይገባል፡፡ እግዚአብሔር እንደገናም፣ “… ኃጢአታቸውንና ዓመጻቸውንም ደግሜ አላስብም” (ዕብራውያን 10፡17) ይላል፡፡ የበደለኝነት ጭጋግ ተገፏል! የእግዚአብሔርን ፍፁም ይቅርታ ተቀበል፡፡

“በክርስቶስ ኢየሱስ ያለው የሕይወት መንፈስ ሕግ ከኃጢአትና ከሞት ሕግ አርነት አውጥቶኛልና፡፡” (ሮሜ 8፡2) የክርስቲያን ሕይወት የነፃነት ሕይወት ነው፡ ማለትም፣ ከኩነኔ፣ እግዚአብሔር እንዳሰበልህ የመኖር እና ከሁሉም በላይ እጅግ አርኪ የሆነው ሕይወት የትኛው እንደሆነ የመለየት ነፃነት ማለት ነው፡፡ ክርስቶስን እየመሰሉ የመሄድ፣ ክርስቶስን የማንፀባረቅ፣ የእድገት ሂደት ነው፡፡ ለማደግም ጊዜ ይወስዳል!

Copyright © 2024. Made by Great Commission Ministry Ethiopia.